Esther 4

መርዶክዮስ የአስቴርን ርዳታ ጠየቀ

1መርዶክዮስ የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም ማቅ ለብሶ፣ በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ አምርሮ እየጮኸ ወደ ከተማዪቱ መካከል ወጣ። 2ማቅ የለበሰ እንዲገባ ስለማይፈቀድለት፣ የሄደው እስከ ንጉሡ በር ድረስ ብቻ ነበር። 3የንጉሡ ዐዋጅና ትእዛዝ በደረሰበት አውራጃ ሁሉ፣ በአይሁድ መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ ጾሙ፤ አለቀሱ፤ ጮኹም። ብዙዎቹም ማቅና ዐመድ ላይ ተኙ።

4የአስቴር ደንገጡሮችና ጃንደረቦች መጥተው ስለ መርዶክዮስ በነገሯት ጊዜ፣ እጅግ ዐዘነች፤ እርሷም በማቁ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። 5ከዚያም አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች መካከል እርሷን እንዲያገለግል የተመደበውን ሀታክን ጠርታ፣ መርዶክዮስ ምን ችግር እንደ ገጠመውና ስለ ምንስ እንደዚህ እንደ ሆነ እንዲያጣራ ላከችው።

6ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። 7መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው። 8አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው።

9ሀታክም ተመልሶ መርዶክዮስ የነገረውን ሁሉ ለአስቴር አስታወቃት። 10እርሷም ለመርዶክዮስ እንዲህ እንዲለው ነገረችው፤ 11“የንጉሡ ባሮችና በንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገባ፣ ንጉሡ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለው ያውቃል፤ ይኸውም እንዲህ ያደረገው ሰው ይገደላል፤ አንድ ሰው ከእንዲህ ዐይነቱ ሞት የሚተርፈው፣ ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ሲዘረጋለት ብቻ ነው። እኔ ግን ወደ ንጉሡ ዘንድ እንድገባ ከተጠራሁ ከሠላሳ ቀን በላይ ሆነ።”

12የአስቴር ቃል ለመርዶክዮስ በተነገረው ጊዜ፣ 13ይህን መልስ ላከባት፤ “አንቺ በንጉሥ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ሕዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይመስልሽ፤ 14በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ፣ ለአይሁድ ርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”

15ከዚያም አስቴር ለመርዶክዮስ ይህን መልስ ላከችበት፤ 16“ሂድና በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ ስለ እኔም ጹሙልኝ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ለሦስት ቀን አትብሉ፤ አትጠጡም። እኔና ደንገጡሮቼም እናንተ እንደምታደርጉት ሁሉ እንጾማለን፤ ይህ ከተፈጸመ በኋላ ግን ነገሩ ምንም እንኳ ከሕግ ውጭ ቢሆንም፣ ወደ ንጉሡ ዘንድ እሄዳለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።”

17ስለዚህ መርዶክዮስ ሄደ፤ የአስቴርንም ትእዛዝ ሁሉ ፈጸመ።

Copyright information for AmhNASV